Reported_02_Feb_2025

ኤልያስ ተገኝ , February 2, 2025

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን የተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች በሚገባ ተደራጅተው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል›› አቶ መልካሙ አሰፋ፣ የማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በስፋት ሥራ ላይ እንዲውል የሚለውን በማሰብ መንግሥት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከማገድ ጀምሮ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ  ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ፣

እንዲሁም ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ ካደረገ ውሎ አድሯል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ኢትዮጵያ በወጠነችው ልክ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋትና ለዚያ የሚሆነውን መሠረተ ልማት ግንባታ በሰፊው ማካሄድ ያለበት ሲሆን፣ በዚህ ላይ በርካታ ነገሮች እንደሚቀሩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ አቶ መልካሙ አሰፋ  የማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ ባለድርሻ ሆነው ከመሠረቱት ኩባንያ በተጨማሪ እንደ ሞኤንኮና ኒሳን ባሉ ድርጅቶች ለረዥም ዓመታት ቁልፍ የቢዝነስና የአውቶሞቲቭ የቴክኖሎጂ የኃላፊነት ሚናዎችን ተወጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በተለይም ከመሠረተ ልማትና ሽያጭ፣ ከመለዋወጫ ዋስትና፣ እንዲሁም ከባትሪ በተጨማሪም ኩባንያቸው ለዘርፉ ካደረገው አስተዋጽኦ ጋር በማያያዝ ኤልያስ ተገኝ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር- በኅዳር ወር በኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 በአረንጓዴ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ሲካሄድ ከተሳተፉ ድርጅቶች ማራቶን ሞተርስ አንዱ ሲሆን፣ እርስዎ ደግሞ ከፓናሊስቶች መካከል ነበሩ፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው የግሪን ትራንስፖርት እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ መልካሙ- በኅዳር ወር የተካሄደው ትልቅ ኤክስፖ ነበር፡፡ ብዙ የአፍሪካ አገሮችን ያሳተፈ ነው፡፡ አገር ውስጥ ያሉንን የኢንዱስትሪ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ከታዳሽ ኃይል ጋር በተያያዘ የሠሩ አካላትም የተሳተፉበት ነበር፡፡ ኤክስፖው በዋናነት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ባለቤትነት የተዘጋጀ ነው፡፡ ኩባንያችን ማራቶን ኢንጂነሪንግ  ከዝግጅቱ ጀምሮ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ፋና ወጊ በመሆኑ ከሚኒስቴሩ ጋር አብሮ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከኢትዮጵያ አልፈን ለአፍሪካም አርዓያ መሆን ስላለብን ይሄንን አድርገናል፡፡ ኤክስፖው ከተጠበቀው በላይ እጅግ በጣም ሰፊና ብዙ ተዋንያን (በኤሌክትሪክ መኪና ተሽርካሪ ላይ የተሳተፉ አስመጪዎች) ተሳትፈዋል፡፡ አገር ውስጥ ያሉ የተሽከርካሪ ገጣጣሚዎችም ነበሩ፡፡ አንድ ያየሁት ስኬት ምንድነው? ... 2020 እኛ ስንጀምር ለመጀመሪያው የኤሌክትሪክ መኪና እጅግ በጣም ፍራቻ ነበር፡፡ ምክንያቱም ታዳሽ ኃይልን፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ስናስብ ስሙም ኮረንቲ ነው ያስፈራል፣ ኅብረተሰቡም ለመቀበል እንዲችል ብዙ የደከምንበት ጊዜ አለ፡፡ የማይቀረውን ቴክኖሎጂ መፍራት የለብንም ብዬ ብዙ መግለጫዎችን በመገናኛ ብዙኃን ቀርቤ አስረድቻለሁኝ፡፡ ኢትዮጵያ ያላት ዕምቅ የሆነ ታዳሽ ኃይል አለ፡፡ ከዚህ መውጣት አለብን፣ እንላመድ ስንል ብዙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ዛሬ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ኢትዮጵያ ውስጥ 70 እስከ 80 ሺሕ የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ገብተዋል፡፡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በአሥር ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ውስጥ የኤሌክትሪክ መኪና 248 ሺሕ ይደርሳል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡

አሁን ግን ከዚያ አስቀድሞ በፍጥነት እዚህ ደረጃ ደርሷል፡፡ ዛሬ መንገድ ላይ እነዚህን ሁሉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በማግኘታችን በግሌም እንደ ኩባንያም ደስተኞች ነን፡፡ የእኛ ኩባንያ ትልቁ ስኬት ምን ያህል አምርቶ ለገበያ አቀረበ የሚለው ሳይሆን፣ በአገራችንና በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በፍጥነት ተላምደው ማየታችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ በኤክስፖው በጣም በርካታ ብራንዶች፣ ምናልባትም ከእነዚህ የተለያዩ ብራንዶች 90 በመቶ የሚሆኑት አንድ ዓይነት ናቸው፣ ቅር ያሰኛል፡፡ ከአንድ ምንጭና ከአንድ አገር የመጡ ናቸው፡፡ ይህ ሲሆን አንድ ዓይነት ዲዛይን (ስፔስፊኬሽን) ጥራትና ሥሪት ነው ስለዚህ ምርጫ ለኅብረተሰቡ አልሰጠም ማለት ነው፡፡ የኤሌክትሪክ መኪና ከመምጣቱ በፊት የካርቦን ልቀቶች መጠን በግራም እያነሱ መጥተዋል፡፡ ሰዎች አላስተዋሉም እንጂ ድሮ የሚወጣውን ጭስ ብዙ አናየውም፣ እያነሰ ነው የመጣው፡፡ በመጨረሻ ወደ ባትሪ ቴክኖሎጂ ተደረሰ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ኃይድሮጂን (ፊዩል ሴል) መጥቷል፡፡ በኤግዚቢሽኑ የቻይና መኪኖች ገበያ ውስጥ ለመግባት በብዛት መጥተዋል፡፡ ነገር ግን የአውሮፓ ብራንዶች አለመምጣታቸው ቅር ያሰኛል፣ የጃፓንና የአሜሪካ ውጤቶች አለመኖራቸው ቅር ያሰኛል፡፡ እኛ ከኮሪያ ስላለን ተዋንያኑ ቢኖሩ የኤሌክትሪክ መኪኖች አንድ ላይ መጥተዋል እንላለን፡፡

ሪፖርተር- ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ ወደ አረንጓዴ ትራንስፖርት እንድትገባ የሚያስችል ሥርዓትና የሀብት አቅም ነበረ? አሁንስ ያለው አቅም ምን ይመስላል?

አቶ መልካሙ- አፍሪካ ውስጥ ምናልባት አንድ አገር ሲሼልስ ደሴት ስለሆኑ፣ ብዙ ጊዜ የኤሌክትሪክ መኪና የሚበዛውና የሚመረጠው በደሴቶች ነው፡፡ የመንገዱ ርዝመት አጭር ስለሆነ ከአንድ ጥግ ወደ አንድ ጥግ ሲደርስ ቻርጂንግጉ በጣም ይንቀሳቀሳል (Shuttle) ያደርጋል፡፡ ትልቁ ጥቅሙ ይህ ነው፡፡ የእኛ አገር የቆዳ ስፋቱን እናውቀዋለን፡፡ አዲስ አበባን እንኳን ብንወስድ እጅግ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከቻርጂንግ ስቴሽንና ከሌሎችም ነገሮች ጋር ተያይዞ ይሆናል አይሆንም የሚል ሥጋት አለ፡፡ ኅብረተሰቡም ልክ ነው፡፡ በእኛ በአምራቾችም በአስመጪዎችም የተፈጠረው ሥጋት ልክ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ መሠረተ ልማት በጣም ወሳኝ ስለሆነ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሳይሆን በመቅረቱ የነበረው ሥጋትና ጫጫታ ልክ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ አሁን የሚቀረን ነገር ይኖራል ልክ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከአፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያ ትልቋ ናት፡፡ ብዙ ተሽከርካሪዎች የገቡባት አገር ናት፡፡ ይህንን ቅድሚያ በመውሰድ ነው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም (PIDA) አያይዞ በመሪነት ወስዶ ነው ይህንን ኤክስፖ ያዘጋጀው፡፡

... 2020 የመጀመሪያዋን አዮኒክ የኤሌክትሪክ መኪና ፋና ወጊ ሆነን በቤተ መንግሥት ያስተዋወቅነው እኛ ነን፡፡ ሁለተኛውን ደግሞ 2021 ኮና መልታይ የሆኑ ሞዴሎችን አወጣን፡፡ ከዚያ ወደ ገበያ ውስጥ በስፋት መግባት ሲጀመር የመሠረተ ልማት ጥያቄ መጣ፡፡ ማራቶን ሞተር ኢንጂነሪንግ ደፍሮ ያን ያህል ካደረገ፣ የቻርጂንግ ጣቢያ አቋቁመን 30 ደቂቃ ሙሉ ቻርጅ የሚያደርገውን ካስገባን፣ መንግሥት ደግሞ በመሠረተ ልማት ግንባታው ለምን አልፈጠነም ነው የእኔ ጥያቄ፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ ውይይት አድርገናል፣ በተደጋጋሚ አስጎበኝተናል፡፡ ብዙ አድርገናል፣ ምክንያቱም ወደኋላ ከተሄደ ብዙ ችግር ያመጣል፡፡ የፖሊሲም ችግር ያመጣል፣ ኅብረተሰቡም ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ስለዚህ የንግድ ቻርጂንግ ጣቢያዎች ካልኖሩ ቤት ቻርጅ እያደረግን የቤት መኪና መንዳት ይቻላል፡፡ ይሁንና የንግድ ታክሲ ማድረግ አይቻልም፡፡ ስለዚህ በየመንገዱ የመሙያ ጣቢያ ያስፈልጋል፡፡ ከመንግሥት ጋር ብዙ እየተነጋገርን ትንሽ ቆም አልን፣ አንዱ ምክንያታችን ይህ ነበር፡፡ ቆም አልን ስንል የኤሌክትሪክ መኪና አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ በመጣነው ሁኔታ አልሄድንም ለማለት ነው፡፡

መንግሥትም በዚህ ልክ ስለገባው ኤክስፖና ውይይት አዘጋጅቶ የተለያዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተለይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ሌሎች ታሪፍ የሚያወጡ አካላት ውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ ሲባል የነበረው ኢነርጂው አለ፣ ታሪፍ ግን አልወጣለትም፡፡ ኢነርጂ መሸጥ ማለት ልክ ማደያ ሄደን ጋዝ እንደምንሸጠው ማለት ነው፡፡ እንደዚያ ነው መሸጥ ያለበት፡፡ በሌላ አገር እንደዚያ ነው፡፡ ይህ ለኢትዮጵያም ለሥራ ፈጠራና ለሌሎች የተለያዩ ነገሮች ይጠቅማል፡፡ አሁን የሆነው ሰው ለመደና መኪኖች ማስገባት ፈጠነ፡፡ መንግሥት ግን ወደኋላ ቀረ፡፡ አሁንም ይህ መሠረተ ልማት ሳይጠየቅ መቶ በመቶ በነዳጅ የሚሠሩ አሽከርካሪዎችን ማገድ ልክ አይደለም ነው የምለው፡፡ ይዘጋጅና ከዚያ አይግባ በማለት ሁሉንም መዝጋት ይቻላል፡፡ ግን አንድ ነገር ስታመጣ ጎን ለጎን በትንሹ አድርገህ መሄድ አለብህ፡፡ ለእኛ አልተዘጋም አምራቾች ስለሆንን፡፡ አንደኛ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚመራው ንቅናቄ አለ፡፡ በዚያ በቤንዚን የሚሠሩ መኪናዎች እየተመረቱ ነው፡፡ ግን ሙሉ በሙሉ ለሚያስመጡት ግን ተከልክሏል፣ ባይደረግ ጥሩ ነው፡፡ ከሆነም ግን እያላመድን አንዱ በአንዱ እየተተካ መሆን ነው ያለበት፡፡ በዓለም በኤሌክትሪክ መኪና ቀዳሚ የሆነችው ኖርዌይ ... 2025 ሽፋኑን 90 በመቶ፣ 2027 መቶ በመቶ ለማድረስ አስባለች፡፡ እዚህ የደረሱት የዛሬ 20 እና 15 ዓመታት ጀምረውት ነው፡፡ የእኛ አብዮት ባይሆን ጥሩ ነው የምለው፡፡

ስለዚህ በኤክስፖ ወቅት በነበረው የፓናል ውይይት ጥሩ ነገሩ ምንድነው? ቢያንስ መንግሥትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ለመውሰድ ገብቷቸው ውይይቱን አዘጋጅተዋል፡፡ ይህ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ትልቁ ችግር ምንድነው? ከዚያ በኋላ ምንድነው የቀጠለው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ኃላፊነት ወስዶ እንደሚሄደው መንግሥትም መፍጠን አለበት፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ 100 የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች ይመጣሉ ተብሏል፡፡ ወይ ገብተውም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቅድም ያልናቸው ፈጥነው መምጣት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር- ስለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሲነገር የባትሪ ጥራት፣ ደኅንነትና አስተማማኝነት በዋናነት ይነሳል፡፡ አወጋገዱን ጨምሮ በዚህ ላይ ልብ ሊባሉ የሚገባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

አቶ መልካሙ- ስለመኪና ሲገለጽ ጥራት (Qulaity) ለረዥም ጊዜ አገልግሎት መስጠት (Durability) እንዲሁም አስተማማኝነት (Reliablily) የሚሉት ጉዳዮች ወሳኝ ናቸው፡፡ በእኛ አገር መኪናን እንደ ሌሎች አገሮች ለአምስት ዓመታት አሽከርክረህ የምታስወግደው ነገር አይደለም፡፡ ለሃያና ለሰላሳ ዓመታት የምታስቀምጠው፣ ሲቸግርህ የምትሸጠውና የምታስይዘው ነው፡፡ የአንድ መኪና ባትሪ ጥሩ ከሆነ ከስምንት እስከ አሥር ዓመታት ነው የሚቆየው፡፡ ይህ ምንም መደበቅ የለበትም፡፡ ለዚያ ነው የስምንት ዓመት ዋስትና የምንሰጠው፡፡ እሱን ደግሞ ኃላፊነት የሚሰማው ኩባንያ ሲሆን ነው፡፡ ሌሎቹ ዘንድ ብትሄድ አይሰጡህም፡፡ ምክንያቱም ከሾው ሩም ገዝተው ነው የሚያመጡት፡፡ ዋስትና የሚሰጥህ አምራች ብቻ ነው፡፡ ለዚያ ነው በውይይቱ ጊዜ ኃላፊነት ያስፈልጋል፣ ዋስትና ያስፈልጋል፣ ሕጋዊ የሆነ አስመጪና አከፋፋይ ያስፈልጋል፣ ይህንን ዓይታችሁ ግዙ የተባለው፡፡ ስምንት ዓመት ወይም 160 ሺሕ ኪሎ ሜትር ሲነዳ የባትሪ ችግር ከመጣ የመተካት ኃላፊነት አለብን፡፡ ምክንያቱም ለኤሌክትሪክ መኪና ወሳኙ ባትሪ ነው፡፡ መደበኛ መኪኖች ያለ ሞተር ቀፎ እንደሆኑ ሁሉ፣ በኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ ባትሪም ተመሳሳይ ነው፡፡ ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ አየር ንብረት በጣም ጥሩ ነው፡፡ ኃይለኛ ሙቀትም አደገኛ ነው፡፡ አንዳንድ የምፈራቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አሁን እንደ ኤርታሌና ጋምቤላ ‹‹ፐብሊክ ባስ›› ቢሄድ እፈራለሁ፣ ሙቀቱ አይቻልም፡፡ የባትሪ ዓይነትም ወሳኝነት አለው፡፡

ሊቲየም አዮን ባትሪ ይመረጣል፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ እንዲህ ነው ማለት ባልችልም ከገቡት መኪኖች ሁሉ የምፈራቸው አደጋዎች አሉ፡፡ በተለይ አስቀድመው የገቡት ላይ ፍራቻ አለኝ፡፡ ዛሬ የእነሱ ባትሪ ቢለካ መቶ በመቶ የነበረው እርግጠኛ ነኝ አሁን 30 ወይም 40 በመቶ ላይ ነው ያለው፡፡ ባትሪውን በኋላ የምንጥልበት ነው የሚጠፋን፡፡ ይህ ሥጋት አለኝ፡፡ የባትሪ ጥራት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ እሺ ባትሪ ተካን እንበል፣ ያገለገለውን የት ነው የምናስወግደው? ማስቀመጫ ቦታን በተመለከተ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ነው የምናደርገው ወይስ ምን?

መንግሥትም ይህንን ካሳበ በጣም ጥሩ ድጎማ ያስፈልጋል፡፡ ታክስ ላይ እንደተደረገው ለእኛ ለአምራቾች 15 በመቶ ቫት አለ፣ ለሌሎቹ አምስት በመቶ አለ፣ 20 በመቶ አለ ማለት ነው፡፡ ቫት የሚደረጉ ታክሶች ሁሉ መደበኛ መጠናቸው (Nominal Amount)  ከፍ ያለ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ከሌላ አገር ጋር ሲወዳደር ጥሩ ማበረታቻዎች አሉን፡፡ ችግሩ እስካሁንም ለኤሌክትሪክ መኪና የምንከፍለው ወይም የምናመጣቸው ክፍሎች ውድ ናቸው፡፡ አንድ የኤሌክትሪክ መኪና ከውጭ ስታመጣ የምታወጣውን ምናልባት ሦስት ወይም ሁለት የቤንዚን መኪና ታስመጣበታለህ፡፡ ምክንያቱም ባትሪው በጣም ውድ ስለሆነ፡፡ ነገር ግን እዚህ ደግሞ ሲመጣ የኤሌክትሪክ መኪና አገር ውስጥ ስትሸጠው ታክስ ስለሌለው ዋጋው ይወርዳል፡፡

ሪፖርተር- በዚህ ወቅት በአምራቾችም ሆነ በአስመጪዎች በገፍ የገቡ ተሽርካሪዎች በስፋት በጎዳና ላይ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ከዋስትናና ከጥገና ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ሥጋቶች አሉ፡፡ ከድኅረ ሽያጭ ጋር ተያይዞ እነዚህ ተሽርካሪዎች ምን ዓይነት ክትትል ይፈልጋሉ?

አቶ መልካሙ- ቅድም ባልኩት ኤክስፖ ብዙ መኪኖችን ዓይተናል፡፡ መኪኖችን እንዳየንና ሁሉም ሊሸጥ እንደመጣው ተመሳሳይ መሠረተ ልማት በዚያው ልክ መታየት አለበት፡፡ በዚያው ልክ ኃላፊነት የሚወስድ ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም በግለሰብ ደረጃ መኪና እያስመጣ በየቤቱ እያጠረ ይሸጣል፣ ወይም ስምንተኛ ፎቅ ቁጭ ብሎ ይህንን ያህል ክፈል ይልሃል፣ ነገ አታገኘውም፡፡ ከየት ነው የምታመጣው ስትለው፣ ከዚህ ከዚህ ይልሃል፡፡ ነገር ግን ሊሸጥልህ ነው እንጂ በዋስትና፣ ከሽያጭ በኋላ ባለው ነገር ላይ ኃላፊነት አይወስድም፡፡ በነገራችን ላይ የኤሌክትሪክ መኪኖች እንደ ቤንዚን መኪኖች ሁሉ የተለየ ራሱን የቻለ ወርክሾፕ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የቤንዚን መኪኖች በሚሠሩበት ቦታ በምንም ዓይነት ሁኔታ የኤሌክትሪክ መኪና ኢንስፔክሽን አይሠራም፣ አደገኛ ነው፡፡ የሚሠራበት/የሚጠገንበት ወለል የተለየ ወይም ታይልስ ስለሆነ፡፡ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ መኪና የሚገዛ ሰው አውቆ መግዛት አለበት፡፡ ከወርክሾፕ ሌላ ባትሪውን የሚሸከም መሣሪያ ያስፈልጋል፡፡ ቴክኒሻኖች ባትሪውን ወይም መኪናውን ሰርቪስ በሚያደርጉበት ጊዜ ኢንሱሌትድ [የተሸፈነ] መሣሪያ/መገልገያ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ለዚያ ደግሞ በክህሎት የተደገፈ ሥልጠና ያስፈልጋል፡፡ ያንን የሚያነቡ የመመርመሪያ ዕቃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ራሱን የቻለ ኢንቨስትመንት ነው እንጂ አስመጥተን ቤታችንን አጥረን የኤሌክትሪክ መኪና ይህ ነው ብለን እያሳየን የምንሸጠው አይደለም፣ ኃላፊነት ያስፈልጋል፡፡ ድኅረ ሽያጭ አገልግሎት፣ ምክርና ዋስትና ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ሲኖሩ ነው ተሻገረ የምንለው፡፡ መሠረተ ልማቶች ማለትም ወደ 280 ቻርጂንግ ጣቢያዎች በቅርቡ ይመጣሉ ተብሏል፡፡ ስለዚህ በዚህ መሀል የሚመጡት ነገሮች ሁሉ መስተካከልና መሟላት  አለባቸው፡፡ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ብዙ ጊዜ 20 በመቶ ሳይወርድ ነው ቻርጅ መደረግ ያለበት፡፡ ከዚያ ደግሞ እስከ 80 በመቶ፡፡ 20 እስከ 80 በመቶ ፈጥኖ ይሄዳል፡፡ 80 በኋላ ያለው ሰዓት ሰፊ ጊዜ ነው የሚወስደው፣ ያዝ ያደርገዋል፡፡ ዕድሜውን እንዳያሳጥረው ማለት ነው፡፡ ይህንን ሁሉ በተመለከተ ሥልጠና መሰጠት አለበት፡፡

እኛን በተመለከተ ብትጠይቀኝ የካቲት ወር መግቢያ አካባቢ 550 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሄዱ ሁለት ባትሪ ሞተር ‹‹ኮና›› የተባለውን በሰፊው አስገብተን እየተገጣጣመ ነው፡፡ ከእሱም አልፎ ‹‹አዮኒክ-5›› የሚባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ገብተዋል፣ ይህንን እናስመርቃለን፡፡ በዚህ ደረጃ እየሠራን ነው የቆየነው፡፡ ከሃንዳይም ጋር የሠራነው ይህንን ነው፡፡ እኔም በውይይቱ ላይ ያነሳሁት ዋስትና፣ ድኅረ ሽያጭ አገልግሎት፣ ምክር፣ በመንግሥት በኩል መሠረተ ልማት ያስፈልጋል የሚለውን ነው፡፡ ምክንያቱም ስለኤሌክትሪክ መኪና፣ እንዲሁም ስለባትሪ ስናወራ ጥራት እጅግ በጣም ወሳኝነት አለው፡፡ በቂ ዕውቀትና ሥልጠናም ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ መኪኖች ጋር ተያይዞ ታክስ ብቻ ሳይሆን፣ በሌላውም ማለትም መስተንግዶና ኢንሹራንስም ላይ ምክንያታዊ መሆን፣ ሰሌዳ ሊወጣ ሲኬድም አብሮ መታጀል የለበትም፡፡

ለደንበኛ ዝም ብሎ መኪናውን መስጠት ሳይሆን እንዴት መጠቀም እንዳለበት፣ አደጋ ቢመጣ ምን ማድረግ እንዳለበት የአስመጪው ወይም የሻጩ ኃላፊነት ነው፡፡ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎችም አልፎ ተርፎ ሥልጠና መሰጠት አለበት፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥት የሚሠራው አለ፡፡ አስመጪዎች፣ አምራቾች፣  ገጣጣሚዎች ወይም ሻጮች የሚሠሩት አለ፡፡ ኅብረተሰቡም በዚያ ልክ ማወቅ ያለበት ነገር አለ፡፡ በአጠቃላይ ግን ኅብረተሰቡ በልበ ሙሉነት ገዝቶ የሚጠቀምበት መሆን አለበት፡፡ አንድ የተረዳሁት ነገር ምንድነው? ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አካባቢ ፖሊሲ አውጪዎቹ ተረድተውታል፡፡ ነገር ግን ታች ሲወረድ እስከ ሰሌዳ የሚወጣበት ክፍል ግንዛቤ ተወስዷል ወይ? እንደዚህ ዓይነት ነገሮች መጥራት አለባቸው ነው የምለው፡፡  

ሪፖርተር- መንግሥት በነዳጅ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ተሽከርከሪዎች ላይ ዕገዳ ጥሏል፡፡ ያንንም ተከትሎ በተለይ ያለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በቂ መሠረተ ልማት ሳይገነባ፣ የመለዋወጫ በቂ አማራጭ ሳይኖር በገፍ መኪኖቹ እንዲገቡ መደረጋቸውን የሚተቹና ‹‹ፈረሱ ጋሪው ቀደመ›› የሚሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን የኤሌክትሪክ መኪና ሲታሰብ ማዕከል እየተደረገ ያለው ከተማ ወይም አዲስ አበባ ብቻ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በዚህ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ምንድነው?

አቶ መልካሙ- ኢሞቢሊቲ ስናስብ ስማርት ሞቢሊቲና ስማርት ሲቲ አሉ፡፡ ስማርት ሲቲ ስትል ስማርት የሆነ መንገድ፣ ተሽከርካሪ (ሞቢሊቲ) ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የሕንፃው ዲዛይንና መንገድ ነው፡፡ ከእነዚህ ጋር አብረው የሚሄዱ ፓኬጆች ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ይህ ነገር በሙሉ አገሪቱ ካልመጣ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ወደ እኛ አገር ስንመጣ ከኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎች 80 በመቶ ማለት ይቻላል አዲስ አበባ ነው ያሉት፡፡ በተለይ የግል፡፡ ከአገሪቱ ውስጥ 85 በመቶ መኪና የግል ሲሆን፣ 15 በመቶው የሚሆነው ብቻ ነው የሕዝብ ትራንስፖርት ብዬ ነው የምገምተው፡፡ 85 በመቶ አዲስ አበባ ነው ያለው፡፡ ይህ ሥራ በአዲስ አበባ መጀመሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ወደ ክልል የሕዝብ (ፐብሊክ) ትራንስፖርቶች አሁን የሚመጡ አውቶቡሶች ስላሉ ማስፋፋቱ ቀላል ነው፣ ደግሞም ይችላል፡፡ ምክንያቱም ምን ያህል መኪና ነው ከመሃል አዲስ አበባ ወደ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምሥራቅና ምዕራብ የሚንቀሳቀሰው? በቀን እንቁጠር ብንል በእርግጠኝነት 200 አይበልጡም፡፡ ለምሳሌ ከዚህ እስከ ሐዋሳ ባለው መንገድ 100 የሚደርሱ የነዳጅ ማደያዎች አሉ ብንል፣ ቢያንስ አሥር በሚሆኑት ትራንስፎርመርና፣ ቻርጂንግ ስቴሽን ቢደረግ በቀላሉ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል፡፡ የዕይታ ጉዳይ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ የኤሌክትሪክ መኪና ከታየ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ መኪና ወይም ታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ሆናለች ብለን ካሰብን ጥሩ አይደለም፡፡ ለማሳየት መሆን የለበትም ማዳረስ መቻል አለብን፡፡ ለምሳሌ በውይይቱ ጊዜ የክልል ከተሞች ከንቲባዎች ነበሩ፡፡ የተለያዩ ጥያቄዎችም ተነስተው ነበር፡፡ እነሱም መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ለትራንስፖርት የሚያመች ቦታ ማዘጋጀት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር- ከዚህ ቀደም ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተገናኘ ለቻርጂንግ ስቴሽኖች የሚሆኑ ዕቃዎች ከታክስ ነፃ እንዲሆኑ መንግሥት ትኩረት ይስጠን ስትሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለጥያቄዎቻችሁ መልስ ተገኘ ወይስ እንዳለ ነው? ይህ ዘርፍ ምን የተለየ ድጋፍ ይፈልጋል?

አቶ መልካሙ- እኛ መጀመሪያ መኪና አስመጥተን የምንሸጥ ቸርቻሪዎች ነበርን፡፡ ከዚያ ነው እስከ መቼ ብለን ወደ መገጣጠሚያ ፋብሪካ የገባነው፡፡ ስንጀምር አምስት ሺሕ መኪና ነበር በዓመት የመገጣጠም አቅማችን፡፡ ይህን በምናደርግበት ጊዜ አምስት የቴክኒክና የሥልጠና ማዕከላትን አቋቁመን ከመላው አገሪቱ የዩኒቨርሲቲ፣ የቴክኒክና የሙያ ተማሪዎችን ወሰድን፡፡ ሥልጠና ከሰጠን በኋላ መጀመሪያ የመጡትን ስድስት የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገራቸው መለስን፡፡ ይህንን ስናደርግ ቅልጥፍናችን ጨመረና አሥር ሺሕ መኪኖች መገጣጠም ደረጃ ላይ ደረስን፡፡ አሁን 20 እና 30 ሺሕ ደርሰናል፡፡ ስንቸገር የነበረው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነበር፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ በፊት 100 ሺሕ ዶላር ለማግኘት አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ለማስቀመጥ ለማድረግ ተገደናል፡፡ ባንክ ማስቀመጥ አለብን፡፡ ሃያ ሺሕ መኪና በዓመት ለመገጣጠም እያሰብክ አንድ ሚሊዮን ዶላር ለመኪና ኢንቨስትመንት ምን ይሠራል? ይህ ሁሉ የመሥሪያ ካፒታል አስይዘህ እንዴት ነው የምትሠራው? ሌላ አገር ይህንን ያህል ካሽ አይያዝም፡፡ ብድር ይመቻቻል፡፡ ሃያ ሺሕ መኪና የማምረት አቅም እያለን አንድ ሺሕ እንኳን ማምረት አልቻልንም ነበር፡፡ ይህችን ትንሽ አምስትና ሰባት በመቶ እያመረትን ነው ለአምስት ተከታታይ ዓመት ማራቶን ሞተርስ የወርቅ ተሸላሚ የሆነው፡፡

ዛሬ ባንኮች ዶላር እየደወሉ ውሰድ ይላሉ፣ ግን አልወሰድንም፡፡ ለምን ቢባል ከውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ በኋላ እኔ ዶላር ባገኝም እኔን የሚገዙኝ ሸማቾች (ኩባንያም ሆነ ግለሰብ) ነጋዴም በለው በዚያ ልክ ገቢው መሻሻል አለበት፡፡ ለምሳሌ  ከውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ በፊት ሦስት ሚሊዮን ብር የነበረ መኪና አሁን 4.5 ሚሊዮን ወይም አምስት ሚሊዮን ብር ይገባል፡፡ ያንን ልዩነት ከየት ያመጣል? ባንክስ ከየት ያመጣል? አሁን ችግሩ ብር ነው ዶላር አይደለም፡፡ እዚህ ያለውን ያስገባነውን ዕቃ በምንፈልገው ልክ ሸማቹ በፊት በነበረው ዋጋ መግዛት (Afford) ማድረግ ስላልቻለ ገበያው ዝም ብሏል፡፡ በእርግጥ እኛ ገበያ አጣን ብለን በሬዲዮም በጋዜጣም አልተናገርንም፡፡ እስካሁንም ደንበኛ አለን እየሸጥን ነው፡፡ ነገር ግን የማየው ነገር አለ፡፡ ይህም መኪና እየፈለጉ የሰረዙ ሰዎች አሉ፣ በጀት ስላልሞላ፡፡ ውኃ ልካችን መምጣት አለበት፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ሪፎርሙ በፊት አሥር ክፍሎችን ማምጣት የምችለውን ዛሬ ባለኝ የመንቀሳቀሻ ካፒታል አምስት ነው የማደርገው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ችግር የለም፣ ግን ደግሞ ሸማቹ አቅሙ በርትቶ ሲመጣ ማጠሩ አይቀርም፡፡ ምናልባት የካፒታል ገበያው ሲከፈት ይህንን ለውጥ ያምጣ አያምጣ አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ያው ስቶክ ማርኬት ባንክ ከምትሄድ ሸጠህ የገንዘብ እጥረትን ያሻሽላል የሚል ነው ዓላማው፡፡ ይህ በምን ያህል ሁኔታ ፈጥኖ ይመጣል የሚለውን የምናየው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር- የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ መመርያ ከማዘጋጀት ጀምሮ ዘርፉ የተለየ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል፡፡ በዝግጅት ያሉ ነገሮች አሉ ወይስ እንደ ባለድርሻ አካል የምታውቁት ነገር የለም?

አቶ መልካሙ- ምንም ጥያቄ የለውም ያስፈልጋል፣ ቅድም ያልኩት እሱን ነው፡፡ ምክንያቱም የኤሌክትሪክ መኪና ራሱን የቻለና ለየት ያለ ነው፡፡ ከሾው ሩሙ ጀምሮ ሥልጠናው ለብቻ፣ ወርክሾፑ ለብቻ፣ መመርዎችና ማበረታቻዎች በደንብ ተደርገው በፖሊሲ ደረጃ መውጣት አለባቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ የሚመለከታቸው ተቋማት ታሪፍ ማውጣት አለባቸው፡፡ ገበያውን እያዩ ለታሪፍ አወጣጥ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን የተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች (ፖሊሲዎች መመርያዎች) በሚገባ ተደራጀተው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ ባትሪው ደግሞ የሚጣል ከሆነ ወይም መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ይህንንም የተመለከተ ብዙ ነገር መሠራት አለበት፡፡ የኤሌክትሪክ መኪና ሲታሰብ ያመጣው ውጤት (ኢምፓክቱ) መታየትና መመዘን አለበት፡፡ የኤሌክትሪክ መኪና አገር ውስጥ ገብቶ አገሪቱም ሆነ ኅብረተሰቡ ምን ተጠቀመ፣ መንግሥትስ የሚለው መታየት አለበት፡፡ አዲስ አበባ ጎዳና ላይ ብዙ የኤሌክትሪክ መኪና ይገኛል ብሎ ቱሪስት እንዲደነቅ ሳይሆን፣ መንግሥት ያሰበውን ዓላማ አንደኛ ነዳጅ ቆጥቧል ወይ? ሁለተኛ የጤና ወጪ (Health Cost) ቀንሷል? ሌላው ደግሞ  ከጥገኝነት ወጥቻያለሁ ወይ (ያው ነዳጅ ፖለቲካ ነው)? የሚሉትን በማለት ለሌሎች አገሮች የሚያሻግር የሚሸጥ ፖሊሲ መሆን አለበት፡፡ በዚያው ልክ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቾችና አስመጪዎችም መጠየቅ አለባቸው፡፡ ዋስትና ለማይሰጥ ኩባንያ መንግሥት ለምንድነው ፈቃድ የሚሰጠው? መጠየቅ አለበት፡፡ አንድ የአውቶሞቢል ነጋዴም ሆነ አምራች ወርክሾፕ አለህ ወይ? ችግርና አደጋ ወይም ግጭት ቢመጣ የት ነው የሚሠራው? ከመንገድ ገዝተህ ማን ነው የሚሠራልህ? በዚያ ልክ ዕውቀት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር- ከዚህ ቀደም ማራቶን ሞተርስ የብዙኃን ትራንስፖርት መኪኖችን ለማምረት፣  እንዲሁም ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ትንንሽ የቤት አውቶሞቢሎችን እናቀርባለን ብላችሁ ነበር፡፡ ይህ ሐሳባችሁ ምን ሆነ? የተያዘውን ዓመት ጨምሮ በመጪዎቹ ዓመታት ከምርትና ከሽያጭ አንፃር ግባችሁ ምንድነው?

አቶ መልካሙ- የኤሌክትሪክ መኪኖችን ብቻ ሳይሆን አምራች ስለሆንን የጋዝ መኪኖችን እየተመረቱ እየተሸጡ ነው ያለው፡፡ ኅብረተሰቡ አይሆንም ሲለን ብቻ ነው የምናቆመው፡፡ ያው የኤሌክትሪክ መኪና ... 2020 ነው የጀመርነው ታሪካዊ የሆነችውን አዮኒክ፡፡  ... 2021 ደግሞ ኮና የተባለውን ሞዴል አቀረብን፡፡ አሁን ሞዴሎች ጨምረን በየካቲት ወር 2017 .. እናስተዋውቃለን፡፡ አያይዘን ‹‹ስታር›› የሚባል የሚኒባስ ተሽከርካሪ ይመጣል፡፡ በጣም ትንንሽ ደግሞ ‹‹ኢንስተር ካስፐር›› የሚባሉ በትራንስፖርት ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ አሉ፣ ምን ያህል ብዛት እንደሚፈለግ በድርድር ላይ ነን፡፡ ከሰኔ በፊት ዋጋቸው በጣም አነስተኛ የሆኑ መኪኖች እናቀርባለን፡፡ አውቶቡሶች ማምጣት እንችላለን፡፡ ከዚያ በኋላ ላመጣነው ኃላፊነት አለብን፡፡ አውቶቡሶች ካመጣን እስከ 350 ኪሎ ቮልት ቻርጂንግ ጣቢያ ይፈልጋሉ፡፡ ከፍተኛ ኃይል ይፈለጋል፡፡ ይህ መዘጋጀት አለበት፡፡ መንግሥት 100 አውቶቡሶች ይገባሉ ስላለ እሱን ካየን በኋላ ይሆናል፡፡

 

News and Events